የፍቅር ሚዛን
የፍቅር ሚዛን በጆኒ በሪሁ "ለአንድ ሳምንት ፍቅረኛዬ ሁን። ከዛ በኋላ ውጪ ሀገር ስለምሄድ አልነዘንዝህም።" ትለዋለች ምስኪኑን ፊሊጶስ። "ሮዚዬ፤ ፍቅርን የሚያህል ነገር እያስመሰሉ መኖር ከባድ ነው። ከዛ በበለጠ ደግም ራስን መዋሸትና መሸወድ ቂልነት ነው" ብሎ ይመልስላታል። ሮዚ ትኩር ብላ ታየውና፤ ፊቷ የተቀመጠው የፊልጶስ ምስል ድብዝዝ እያለ ይሄዳል። ወደ ሐሳብ ዓለም ጠልቃ ትገባለች። ሁለቱ ፍቅረኞች ቢሆኑ ህይወቷ ምን ያህል በፍካት የተሞላና አስደሳች ይሆን እንደነበረ ታሰባት። ዓይኖቿ "ቢሆን" ብላ ስታስበው የቆየችው ሁሉ እንዳልሆነ ሲያውቁ በትኩስ እንባ ረጠቡ። "ለምንድነው ግን እንዲህ የምወድደው?" ስትልም አሰበች። *** ለቤቷ የመጨረሻ ልጅ ነች። ሁሉም እንደ ትንሽ ነበር የሚያያት ከፊልጶስ በስተቀር። ጎረቤታሞች ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ በጨዋታ የምታሳልፈው ከፊልጶስ ጋር ነበር። ልጅ እያሉ እሱ የዋህ ነበር። እሷ ግን በጣም ብልጣብልጥ ነበረች። ሙሉ ቀን "ይህን አድርግ"፣ "ያኛውን ወዲህ አምጣ"፣ "እንዲህ ሁን"... የትእዛዝ መአት። እሱ ያዘዘችውን ሁሉ ያደርጋል። እሷ ይህን ጸባዩ አውቃ፤ ወንድሞቿን እና ጓደኞቿን ጠርታ እንዴት እንደሚታዘዛት ለማሳየት ትሞክራለች። የልጅ ነገር ሆኖ፤ ሁሉም ህጻናት በፊልጶስ ላይ ይስቃሉ። ሮዚም ብትሆን የእሱ መዋረድ የእሷ መከበር እየመሰላት በልጅነት ልቧ ደስ ትሰኝ ነበር። ፊሊጶስ የሚኖረው ከወንድ አያቱ ጋር ነበር። ወላጆቹ በህይወት አልነበሩም። የአባቱን ሚና ወንድ አያቱ ተክተውለት ነበር። የእናቱንና የእህቱን ሚና ግን ማንም የሚተካ ሰው አልነበረም። ጎረቤት ያለችው ሮዚ ስትጠጋው...

