የፍቅር ሚዛን
በጆኒ በሪሁ
"ለአንድ ሳምንት ፍቅረኛዬ ሁን። ከዛ በኋላ ውጪ ሀገር ስለምሄድ አልነዘንዝህም።"
ትለዋለች ምስኪኑን ፊሊጶስ።
"ሮዚዬ፤ ፍቅርን የሚያህል ነገር እያስመሰሉ መኖር ከባድ ነው። ከዛ በበለጠ ደግም
ራስን መዋሸትና መሸወድ ቂልነት ነው" ብሎ ይመልስላታል። ሮዚ ትኩር ብላ ታየውና፤ ፊቷ የተቀመጠው የፊልጶስ ምስል ድብዝዝ
እያለ ይሄዳል። ወደ ሐሳብ ዓለም ጠልቃ ትገባለች። ሁለቱ ፍቅረኞች ቢሆኑ ህይወቷ ምን ያህል በፍካት የተሞላና አስደሳች ይሆን እንደነበረ
ታሰባት። ዓይኖቿ "ቢሆን" ብላ ስታስበው የቆየችው ሁሉ እንዳልሆነ ሲያውቁ በትኩስ እንባ ረጠቡ። "ለምንድነው
ግን እንዲህ የምወድደው?" ስትልም አሰበች።
***
ለቤቷ የመጨረሻ ልጅ ነች። ሁሉም እንደ ትንሽ ነበር የሚያያት ከፊልጶስ በስተቀር። ጎረቤታሞች
ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ በጨዋታ የምታሳልፈው ከፊልጶስ ጋር ነበር። ልጅ እያሉ እሱ የዋህ ነበር። እሷ ግን በጣም ብልጣብልጥ ነበረች።
ሙሉ ቀን "ይህን አድርግ"፣ "ያኛውን ወዲህ አምጣ"፣ "እንዲህ ሁን"... የትእዛዝ
መአት። እሱ ያዘዘችውን ሁሉ ያደርጋል። እሷ ይህን ጸባዩ አውቃ፤ ወንድሞቿን እና ጓደኞቿን ጠርታ እንዴት እንደሚታዘዛት ለማሳየት
ትሞክራለች። የልጅ ነገር ሆኖ፤ ሁሉም ህጻናት በፊልጶስ ላይ ይስቃሉ። ሮዚም ብትሆን የእሱ መዋረድ የእሷ መከበር እየመሰላት በልጅነት
ልቧ ደስ ትሰኝ ነበር።
ፊሊጶስ የሚኖረው ከወንድ አያቱ ጋር ነበር። ወላጆቹ በህይወት አልነበሩም። የአባቱን ሚና
ወንድ አያቱ ተክተውለት ነበር። የእናቱንና የእህቱን ሚና ግን ማንም የሚተካ ሰው አልነበረም። ጎረቤት ያለችው ሮዚ ስትጠጋው ግን
ሁሉም ነገር ተቀየረ። በልጅ ልቦናው ባያስበውም፤ ውስጠ-ስሪቱ ግን አንድ ሙሉእ የሚያደርገውን ሰው እንዳገኘ ይነግረው ነበር። ይህንን
ለመረዳት ፊልጶስ በጣም ልጅ ነበር። ባይረዳውም ግና ጥሩ ስሜት እየተሰማው ስለነበር፤ ከሮዚ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጣት አይፈልግም።
ለዛም ነበር ህጻኑ ፊሊጶስ ህጻኗን ሮዚ ለማስደሰት በጣም ይጣጣር የነበረው።
ሁለቱም ጋር የነበረው ስሜት የጾታዊ ፍቅር አልነበረም። እሷ እንደሌሎች የአካባቢዋ ልጆችና
ጓደኞቿ ትወደዋለች። እሱ ደግሞ እንደ እህቱ ስለሚያያት ከሌሎቹ አብልጦ ይወዳታል። እያደጉ ሲመጡ ግን ሁሉም ነገር እየተቀያየረ
መጣ። ቀድማ ያደገችው ሮዚ ነበረች። ከሌሎች ወንዶች በበለጠ ፊልጶስ እንደሚያስብላት፤ እሷን ለማስደሰት እንደሚጥር እያስተዋለች
ሄደች። ይህ አስተውሎት ደግሞ በልቧ ውስጥ ትንሽዬ ስሜት መፍጠር ጀመረ። ይሄ ትንሽ ስሜት እየተጠራቀመ በጊዜ ሂደት ታላቁን ፍቅር
ሆነ። መጀመሪያ ላይ እያፈቀረችው እንደሆነ ማስተዋል አልተሳናትም ነበር። በእርግጠኝነት እንደምታፈቅረው ስታውቅ ግን ለሁሉም ነገር
ረፍዶባት ነበር። ወደኋላ መመለስ የማትችልበት ነጥብ ላይ ደርሳ ነበር። እሱ ግን ልጅ እያሉ የነበረው ፊሊጶስ ነው። ማደጉ እስካይታወቅ
ባህሪው ተመሳሳይ ነበር።
***
"ሮዚ ሮዚ" እያለ ይነቀንቃት ጀመር ፊልጶስ፤ እሱን ፊቷ ጎልታ በሐሳብ
ዓለሟ ጠልቃ ከነጎደችበት ሰመመን እያባነናት። ወደቀልቧ ተመልሳ እያየችው እንደሆነ ሲያውቅ ፈ..ገ...ግ አለ። በሮዚ ዓይኖች ውስጥ
የነበሩት ትኩስ እንባዎችም ገንፍለው በጉንጮቿ ላይ ፍ..ስ...ስ አሉ። የእንባዎቿ ዘለላዎች ከናፍሯ ላይ ደርሰው ጨው ጨው ጣሟት።
ፈገግ አለች፤ የውስጧን መጎዳት ላለማሳየት። ከኪሷ ውስጥ ሶፍት አውጥታ፤ ፊቷን ያበላሸውን እንባ አበሰች። አስጨንቃ ከጠየቀችው
ምንም ነገር "እምቢ" እንደማይላት ታውቃለች።
"አልቻልኩም ፊሊዬ፤ እየተጎዳሁብህ ነው። እንዳልሞትብህ" አለችው እጆቹን
ይዛ በተማጽኗዊ አተያየት። ፊሊጶስ ተሸነፈ። ሮዚ ከዚህ በላይ ስትጎዳ ማየት አይፈልግም።
"እሺ በቃ ሮዚዬ። በምትይው ሁሉ እስማማለሁ። እንሞክረው በቃ"
የሮዚ የዳመነ ፊት ፀሐይ ወጣለት። እንደኮረኮሩት ህጻን ፊቷ በደስታ ፍልቅልቅ አለ። ፊልጶስን
ተጠጋችው፤ እሱም ራሱን ሮዚን ለማቀፍ አስተካከለ። ሮዚ እቅፉ ውስጥ ገባች። ጥርሷ ብቻ ሳይሆን ነፍሷም ፈገግ አለች።
ፈገግታዋ ግን ብዙም አልቆየም፤ ቀስ እያለ እየደከመ ሄደ። በእቅፉ ውስጥ እንዳለች የልብ
ምቱን አዳመጠች። የተረጋጋ የልብ ምት ነው። የእሷ የልብ ምት ግን ደረቷን ሊሰነጥቅ ደርሷል። አዎ የሁለቱም የልብ ምት ሚዛናዊ
አይደለም። ልኬቱ ተዛብቷል። በረጅሙ ከተነፈሰች በኋላ ዓይኗን ጨፈነች። ስለፍቅሯ አሰበች። የፍቅር ሚዛን ወደእሷ እንዳደላ አውቃለች።
እሷ ግን ሚዛኑ እንደሚስተካከል አመነች። ከገባችበት አስደሳች የፍቅር ዓለም መውጣት አልፈለገችም። ራሷን እያታለለች ቢሆንም፤ በጀመረችው
መንገድ ለመቀጠል ወሰነች። የተዛባውን የፍቅር ሚዛን በራስወዳድነት በኃይሏ አስተካክላ ወደፊት ለመቀጠል ወሰነች።
ከዛም የጨፈነቻቸውን ዓይኖቿን ገለጠች። ጥርሶቿ ፈገግ አሉ። ነፍሷ ግን አልፈገገችም።


It's cool to see how far you came from writing.
ReplyDelete