የፍርሃት ጨዋታ


በጥንት ዘመን አንድ ውጊያ የሚወድ ታላቅ የጦር መሪ ነበር፡፡ በህይወቱ ሙሉም ተሸንፎ አያውቅም፡፡ የሩቅ ሃገር ነጋዴዎችን ሲያጠያይቅ፤ በሰሃራ በረሃ መሃል የምትገኝ አንዲት ትንሽዬ ከተማን ማንም በጦርነት አሸንፏት እንደማያውቅ ሰማ፡፡

ይሄ የጦር መሪ ጀብደኛ ስለነበረ ‹‹ያቺን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፈ የጦር መሪ›› ለመባል፤ ሰፊ ቁጥር ያለውን ሰራዊቱን አደራጅቶና አሰልጥኖ ለጦርነት ተዘጋጀ፡፡ ወደከተማዋም ከሰራዊቱ ጋር ጉዞውን ጀመረ፡፡

ይሄ የጦር መሪ… በሩቅ ሃገር የምትገኝ ትንሽዬ ከተማን ለመውረር ሰራዊቱን ይዞ ሲጓዝ… ብዙ ውሃ ካለበት ኩሬ ይደርሳል፡፡

ከኩሬው ሰራዊቱ ውሃ ሲጠጣ፤ የሙሉ ሰራዊቱን በቁጥር ሲሶ የሚያህሉ ወታደሮች በውሃው መመረዝ ሳቢያ ሞቱ፡፡ የሞቱት ጓዶቻቸውን ቀብረው የተቀሩት ወታደሮች ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡

ከብዙ አድካሚ የእግር ጉዞ በኋላ፤ የሰራዊቱ አባላት ሌላ ሁለተኛ ኩሬ አገኙ፡፡ የመጀመሪያው ኩሬ ላይ በውሃ መመረዝ የሞቱትን ጓዶቻቸውን እያሰቡ፤ ከሁለተኛው ኩሬ ማንኛቸውም ውሃ ሳይጠጡ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ በመንገድ ላይ ጥቂት ወታደሮች በውሃ ጥም ሳቢያ ሞቱ፡፡ ከሃገራቸው ሲወጡ ከነበራቸው ቁጥርም፤ በህይወት የቀረው ወታደር ቁጥር ግማሽ ያህል ሆነ፡፡

አሁንም ብዙ ከተጓዙ በኋላ፤ የሰራዊቱ አባላት ሌላ ሶስተኛ ኩሬ አገኙ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ወታደሮች በውሃ ጥም እየተሰቃዩ ስለነበረ

 

ከኩሬው ውሃ ጠጡ፡፡ ውሃውን የጠጡት ጥቂት ወታደሮች ምንም እንዳልሆኑ ባወቁ ጊዜ የሶስተኛው ኩሬ ውሃ ያልተመረዘ መሆኑን የቀሩት የሰራዊት ክፍሎች ስላወቁ የውሃ ጥማቸውን ከኩሬው በመጠጣት አረኩ፡፡

ሰራዊቱ አሁንም ከረጅምና አድካሚ ጉዞ በሁዋላ፤ ሌላ አራተኛ ኩሬ አገኙ፡፡ ከዛም ኩሬ ውሃ ሲጠጡ ምንም አልሆኑም፤ ውሃው ያልተመረዘ ነበረ፡፡ ከኩሬው ውሃም ጥማቸውን ስላረኩ፤ ሁሉም የሰራዊቱ አባላት ደስ አላቸው፡፡

አሁንም ወታደሮቹ ረጅም ርቀት ከተጓዙ በኋላ፤ ለአምስተኛ ጊዜ ኩሬ አገኙ፡፡ ከኩሬው ውሃ ጠጡ፡፡ አብዛኛው የሰራዊቱ አባላትም ተመርዘው ህይወታቸው አለፈ፡፡ ከሃገራቸው ሲወጡ ከነበራቸው የወታደር ብዛትም ሲሶዎቹ ብቻ በህይወት ቀሩ፡፡

በህይወት የቀሩት የሰራዊት ክፍሎች ብዙ ተጉዘው፤ ሌላ ስድስተኛ ኩሬ አገኙ፡፡ በአምስተኛው ኩሬ ላይ የሞቱ ጓዶቻቸውን እያስታወሱ፤ ሁሉም ከስድስተኛው ኩሬ ምንም ውሃ ሳይጠጡ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ በረጅም አታካች የበረሃ የመንገድ ጉዞ ተዳክመው እና በውሃ ጥም ሳቢያ ብዙ ወታደሮች ህይወታቸው አለፈ፡፡ ከሃገራቸው ሲወጡ ከነበራቸው ቁጥርም አንድ አስረኛ ብቻ የሚሆኑት በህይወት ተረፉ፡፡

ያንን ሁሉ ስቃይ እና መከራ አሳልፈው፤ ሊወርሯት ካሰቧት ከተማ ቁጥራቸው ተመናምኖና ተዳክመው ደረሱ፡፡ የዛች ትንሽ ከተማ ወታደሮችም በፍጥነት የተዳከመውን ሰራዊት ከብበው ሁሉንም ማረኳቸው፡፡

በህይወቱ ተሸንፎ የማያውቀው የጦር መሪም፤ የዛችን ትንሽዬ ከተማ ሰዎች ፤ እንዴት ሊያሸንፏቸው እንደቻሉ ጠየቃቸው፡፡

እነሱም “ወደ እኛ ስትመጡ ከምታገኟቸው ስድስት ኩሬዎች በሁለቱ ላይ ብቻ ነው፤ መርዝ የጨመርነው” አሉት

“በአንደኛው እና በአምስተኛው ላይ ነው አይደል ?” ሲል ጠየቃቸው

“አዎ” አሉት

የጦር መሪው በትንሽዋ ከተማ ሰዎች ብልሃት እጅግ በጣም ተገርሞና ተደንቆ፤ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው ፡-

“የውጊያ ጥበባችሁ እጅግ በጣም አስደናቂ እና ብዙ እውቀቶች ያሉት ነው፡፡ እናንተ ይህንን የውጊያ ጥበብ ምን ብላችሁ ነው የምትጠሩት ?”

ሁሉም የዛች ትንሽዬ ከተማ ነዋሪዎች፤ በታላቁ የጦር መሪ ላይ እየሳቁበት በአንድ ላይ እንዲህ አሉት ፡-

“የፍርሃት ጨዋታ ነው የምንለው፡፡ የፍርሃት ጨዋታ”


Comments

Popular Posts